• +251462204629
  • Hawassa , Ethiopia

ካገለገሉ ተሸከርካሪዎች ሽያጭ የብር 6.5 ሚሊዮን ብር ገቢ ተገኘ

በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል መንግስት ፋይናንስ ቢሮ ከክልሉ አምስት ተቋማት ከአገልግሎት ወጪ ተከማችተው የነበሩ ማሽነሪዎችና ተሸከርካሪዎች ባሉበት ሁኔታ በጨረታ ተሸጧል፡፡ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት ከተካሄደው ከዚህ ሽያጭ ብር 6,552,022.82 ገቢ መገኘቱን አቶ አለማየሁ ሀንዳሞ በቢሮው የጋራ ግዥና ንብረት ማስወገድ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ገልፀዋል፡፡
አቶ ዓለማየሁ አክለውም ከክልል አምስት ሴክተር መስሪያ ቤቶችና ሦስት የክልል ተቋማት በቀረበው መረጃ ላይ ተመሥርቶ 98 ማሽነሪዎችንና ተሸከርካሪዎችን ባሉበት ሁኔታ የመገምገምና መነሻ ዋጋቸውን በባለሙያ የማስገመት፣ የጨረታ ሰነዱን በአጽዳቂ ኮሚቴ የማጸደቅና የጨረታ ሥራዎች ከተከናወኑ በኋላ ሂደቱን በአጽዳቂ ኮሚቴ አጸድቆ ለአሽከርካሪዎች የማስተተላለፍ ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል፡፡
ዳይረክተሩ አያይዘውም ማሽነሪዎችና ተሸከርካሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም ንብረቶች በየሥፍራው ሣር በቅሎባቸው እየተዝረከረኩ ይገኛሉ፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ንብረቶችን ከማስወገድ አንፃር በሚፈለገው መጠን አልተሠራበትም ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ከየመስሪያ ቤቱ ባሰባሰብነው መረጃ የሚወገዱ በርካታ ንብረቶች ያሉ ሲሆን ወደ ማስወገድ ተግባር ሲገባ ንብረቶቹን አሳልፎ በመስጠት ሂደት ቁርጠኝነት እንደሚጎድል ገልጸዋል፡፡
ንብረቶችን ከማስወገድ አንፃር ያሉትን ችግሮች ሲያስረዱም በክልል ደረጃ የባለሙያ እጥረት መኖር፣ በሴክተር መሥሪያ ቤቶች ስለሚወገዱ ንብረቶች ወቅታዊ መረጃ አለመስጠት፣ ሳይወገዱ በተቀመጡ ንብረቶች ላይ ምዝበራ መከሰት ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ፣ ንብረቶች ባለመወገዳቸው ምክንያት ለልማት የሚፈለጉ ቦታዎች ያለሥራ ይዞ ማስቀመጥ ለብልሽት በሚዳረጉ ንብረቶች ምክንያት ለአካባቢ አየር ንብረት ብክለት መጋለጥ ሌላው ችግር ነው በማለት አስተያየታቸውን አጠቃለዋል፡

0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *