• +251462204629
  • Hawassa , Ethiopia

በክልሉ 246 በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት 746 ፕሮጀክቶችን ይዘው በመስራት ላይ መሆናቸው ተገለጸ

በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል መንግሥት በአሁኑ ወቅት 246 የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት 746 ፕሮጀክቶችን ይዘው በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸውን በቢሮው የፊስካል ፖሊሲና ሲቪክ ትብብር ዘርፍ አስታወቀ፡፡
ድርጅቶችና ማኅበራቱ ለዚህ ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ 17.89 ቢሊዮን ብር የመደቡ ሲሆን 73.9 ሚሊዮን ሰዎችን ተጠቃሚ ያደርጋሉ (የሰዎች ቁጥር ከፍ ያለው አንድ ሰው በአንድ በላይ ፕሮጀክት ተጠቃሚ ስለሚሆኑ ነው)፡፡
የፕሮጀክቶች ስርጭት በክፍላተ ኢኮኖሚ ሲታይ ጤና 24.78%፣ የተቀናጀ ልማት 36.56%፣ ትምህርት 12.71%፣ ሴቶችና ሕፃናት 10.59%፣ ግብርና 5.24% እና ውሃ 3.97% ድርሻ አላቸው፡፡
ከአካባቢ ስርጭት አንፃር ከሚካሄዱት ፕሮጀክቶች ሲዳማ 16.22%፣ ሀዋሳ ከተማ አስተዳደር 13.4% እና ደቡብ ኦሞ 9.25% በቅደም ተከተል በመያዝ ከፍተኛ ድርሻ ሲኖራቸው፣ ባስኬቶ፣ ኮንታ እና የም ልዩ ወረዳዎች አንድም ፕሮጀክት የላቸውም፡፡
በቢሮው የፊስካል ፖሊሲና ሲቪክ ትብብር ዘርፍ በተጨማሪ እንደገለጸው በ2012 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ብር 4,282,838,578 በጀት ያላቸው 87 ፕሮጀክቶች የብቃት ግምገማ በማድረግ የውል ስምምነት በመፈራረም ወደ ሥራ እንዲሰማሩ የተደረገ ሲሆን በዚህም ለ957,738 ያህል የህብረተሰብ ክፍሎች ቀጥተኛ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉ ተገልጿል፡፡
ለ76 ፕሮጀክቶች የአጋማሽና የማጠቃለያ ጊዜ ግምገማ የተካሄደ ሲሆን ግብረ-መልስም መሰጠቱ ታውቋል፡፡ የ25 ፕሮጀክቶች ውል ማሻሻያ ጥያቄዎችን መርምሮ የማጽደቅና የመፈራረም ሥራ መከናወኑና ለ25 የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት የሥራ ፍቃድ ውል መፈረሙም
ለማወቅ ተችሏል፡፡ የባንክ ሂሣብ እንዲከፈትላቸው ድጋፍ ለጠየቁ ለ8 አዲስና ነባር የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት አስፈላጊው ድጋፍ መሰጠቱም ተገልጿል፡፡

የበአድማት ኘሮጀክቶች ከቀረጥ ነፃ ድጋፍ አገልግሎት በቀረበው ጥያቄ መሰረት አግባብነቱን ፈትሾ ለመስጠት ታቅዶ ለ2 ፕሮጀክቶች የቀረጥ ነጻ አገልግሎት ድጋፍ ተሰጥቷል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት የሚቀርቡ ከቀረጥ ነፃ ጥያቄዎች በአዋጅ ቁጥር 1113/2011 መስረት ተፈፃሚ የሚሆነው በፌዴራል የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ እንዲሆን መደንገጉ ይታወሳል፡፡
ነገር ግን ይህንን ተግባር ለመፈፀም ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የድጋፍ ደብዳቤ በተለይም የሚቀርቡ ከቀረጥ ነፃ ጥያቄዎች በፕሮጀክት ውል ስምምነት ሰነድ ስለመኖራቸው በማረጋገጥ ተግባራዊ ይሆናል፡፡
በተመሳሳይ ከቀረጥ ነፃ የገቡ ተሽከርካሪ እና ሌሎች ቁሳቁሶችን ከፕሮጀክት ትግበራ መጠናቀቅ በኋላ በፌደራል የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ አማካኝነት እንዲተዳደሩ ተደርጓል፡፡
በዚህም መሰረት የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት በሌሎች አካባቢዎች ፕሮጀክት ካላቸው ያለአንዳች ክልከላ ቁሳቁሶችን አዘዋዉረው እንዲጠቀሙ የሚፈቀድ ሲሆን በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት የሚዘጋ ከሆነ ተመሳሳይ ተግባራት ለሚፈጽሙ ድርጅቶች እንዲተላለፍ የሚደረግ መሆኑ ዘርፉ በተጨማሪ አስታውቋል፡፡

0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *